የሚዲያ ግንዛቤ (Media Literacy)- Part I
| በዚህ ርዕስ ሥር ቀጠሎ የተዘረዘሩ ጒዳዮች እንመለከታለን። 1. የሚዲያ ግንዛቤ (Media Literacy) ምንነትን መረዳት 2. በሚዲያ የሚተላለፉ መልእክቶችን ለመመርመ የሚያስፈልጒ መስፈርቶች መረዳት 3. የእመኑልኝ (Persuasive) ውትወታ ቋንቋዎችን መረዳት |
መግቢያ
ሚዲያዎች ብዙ አሉታዊ ተጽዕኖዎች እንዳሏቸው ከላይ ለማየት ሞክረናል። ችግሮቹ ዘርፈ ብዙና አሳሳቢ በመሆናቸው ብዙ ሰዎች መሸሽን እንደ አማራጭ ይወስዳሉ። ነገር ግን ችግሮችን የምናሸንፈው በመሸሽ ወይም ስለ ሚዲያ አሉታዊ ነገሮችን ብቻ በማንጸባረቅ አይደለም። እኛ መሸሽ ብንፈልግ እንኳን ሚዲያ የማይደርስበት ግራጫ ደሴት የለም። ስለዚህ ያለው ብቸኛ አማራጭ ስለ ሚዲያ በቂ ግንዛቤ መውሰድና በዕውቀት መጋፈጥ ብቻ ነው። በዚህ ርዕስ ሥር የምንመለከተው የሚዲያ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን በመቀነስ እንዴት ለመልካም ነገር ብቻ መጠቀም እንደምንችል የሚያሳዩ መሠረታዊ ግንዛቤዎችን ነው።
| ሚዲያ ግንዛቤ (Media Literacy) |
| የሚዲያ ግንዛቤ ማለት በተለያዩ ሚዲያዎች ማለትም በሕትመት፣ ዲጂታል ወይም በብሮድካስት መልክ የሚቀርበውን መረጃ የመጠቀም፣ የመመርመር፣ የመገምገም እና የመፍጠር ዐቅም ማዳበር ማለት ነው። አንድ ሰው የሚዲያ ግንዛቤ ወይም ዕውቀት አለው የሚባለው እነዚህ ችሎታዎችን በአንድነጥ አጣምሮ የያዘ እንደሆነ ነው። |
ሐሳቡን የበለጠ ለመረዳት ቃሎቹን ለብቻ ነጣጥለው እንያቸው፡
መጠቀም፦ የሚዲያ ግንዛቤ መረጃዎቹ የሚተላለፍባቸው ቻናሎች (መስመሮች)ና ቴክኖሎጂዎችን ከመረዳት ይጀምራል። ይህ ግንዛቤ መረጃን አስሶ በማግኘትና መረጃ የሚገኝባቸው ምንጮችን ወይም የመገናኛ አውታሮችን የመጠቀም ችሎታ ያካትታል። ለምሳሌ የብሮድካስት ሚዲያዎች መካከል ተገቢ የሆኑንት መርጦ ማግኘት፣ የኢንተርኔት አጠቃቀም ክህሎት ወዘት ሊያካትት ይችላል።
በዚህ ሐሳብ ሥር የሚካተቱ ቴክኒኮች
- የመረጃ አፈላለግ ዘዴ
- ስለ ኢንተርኔት መጠቀሚያ (Browser) ሶፍትዌሮች ግንዛቤ ማግኘት
- ስለ መረጃ ማሰሻ ሞተሮች (Search engines) ና አሠራራቸውን ማወቅ
- የመረጃ አፈላለግ ዘዴ ማወቅ
- የኢሜይል አከፋፈተና አጠቃቀም ዘዴዎች
- የኢሜይል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል አንዱን መምረጥ
- ኢሜይል መክፈት
- በኢሜይል መልእክት መለዋወጥ
- ስለ ማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም
- የማኅበራዊ ሚዲያ ዓይነቶችን መምረጥ
- አከፋፈትና አጠቃቀም
መመርመር (Analysis)፦ የመረጃ አፈላለግ ክህሎታችን ከዳበረ በኋላ ቀጥሎ ያለው መሠረታዊ ግንዛቤ የተገኘውን መረጃ የመመርመ ዐቅም ነው። በእጃችን የገባው መረጃ እንደደረሰን ወዲያው ወደ ተግባር ከመለወጣችን ወይም ውሳኔ ከማሳለፋችን በፊት የመልእክቱን ተአማኒነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል። የመረጃውን ተአማኒነት ለመለካት ቀጥሎ ያሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ማረጋገጥ፥-
- የመረጃው አምራች ማን ነው?
- ለምን ዓላማ ነው የተጻፈው?
- ከመረጃው ጀርባ ያለው ሊተላለፍ የተፈለገው መልእክት ምንድን ነው?
እያሉ በጥልቀት መጠየቅን የሚያካትት ነው። ወይም በሌላ በኲል መረጃውን የምናሰራጭ ከሆነ መረጃ የሚሰራጭባቸው መሠረታዊ ቴክኒኮችን ማወቅ ያስፈልጋል። ትኲረት የሚስቡ ቃላት አጠቃቀም፣ የእይታ ምናብ እና ሐሳባችንን የምንተርክበት ዘዴ በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል። ይኸ ግንዛቤ ጤናማ የሆኑ መረጃዎችን ከተሳሳቱ መረጃዎች የምንለይበት አንዱ መንገድ ቢሆንም ትክክለኛውን መረጃ በኀላፊነት ለሌሎች በምናስተላልፍበት ጊዜ መልእክታችንም ጤናማ እንዲሆን ያግዘናል። ብዙውን ጊዜ ጤናማ ያልሆኑ መረጃዎች ወገንተኛና ጥላቻ መልእክቶች ዐዘል ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ዩትዩብ ላይ የሚለጠፉ የቪዲዮ ማስታወቂያዎችን (Thumbnails) ብቻ በማየት የመልእክቱን ጤናማነት መረዳት ይቻላል።