የሚዲያ ግንዛቤ (Media Literacy) Part II
እመኑልኝ ቋንቋ (Persuasive language)
የሚዲያ ትልቁ ትግል የሚተላለፈው መልእክት እውነት እንደሆነ ታዲያሚዎች እንዲያምኑ ማድረግ ነው። ለዚህ ነው ፊልሞች ላይ ወይም ማስታወቂያዎች ላይ የተለያዩ ተጨማሪ የዕይታ መሳቢያ (Visual Effects) ቴክኒኮችን የሚጠቀሙት። የ “እመኑኝ” ዘዴ የሚዲያ ባለሙያዎች የሰዎችን ስሜት ቆንጥጦ ለመያዝ የሚጠቀሙበት ቃላት ናቸው። ብዙውን ጊዜ ከተለጠፈ ማስታወቂያ ጋር ወይም በተንቀሳቃሽ ምስሎች የተደገፈ ሊሆን የሚችል ሲሆን መልእክቱን ያለ ማመንታት እንድንቀበል ወይም ለመልእክቱ ጥሪ ወዲያው ምላሽ እንድንሰጥ የሚያስገድዱ ቃላት ይሆናሉ። እመኑልኝ ባዮች ትኲረት ለመሳብ፣ ተአማኒነትና እምነትን ለማትረፍ፣ ስሜታችንን ለመቀስቀስ፣ በሐሳባቸው እንዲንስማማ ለማድረግ ይህንን ዘዴ ይጠቀማሉ።
በብዛት ሥራ ላይ የሚውሉ የእመኑልኝ ቴክኒኮች
- አጣምሮ (Association)
ሊተላለፈ የተፈለገው መልእክት ወይም ማስታወቂያ በማኅበረሰቡ ዘንድ ዕውቅና ካገኘ ነገር ጋር ወይም ተወዳጅ ነገር ጋር አጣምሮ ማቅረብ ነው። ለምሳሌ የቢራ ማስታወቂያዎች ከደስታ ወይም መዝናናት ጋር ያጣምሩታል። የኮካ ማስታወቂያ ከቤተሰብ ጋር፣ ናይክ ማስታወቂያ ከድል ጋር ማጣመር።
- ተመሳሰል (Bandwagon)
ብዙዎችን ያንን እያደረጒ ነው፣ ወይም እየገዙ ነው፣ ስለዚህ አንተም ተቀላቀላቸው።
- ቆንጆ ወይም ታዋቂ ሰዎች
በብዛት የሚታወቅ የማስታወቂያ ዘዴ ነው። በፊልም ወይም በዘፈን የሚታወቁ ሰዎችን መጠቀም።
- አስፈራርቶ
ሰዎች ውስጥ ፍርሃት ካሰራጩ በኋላ መፍትሄ እነሱ ጋር እንዳለ ማሳሰብ። በተለይ ፖለቲከኞች በብዛት ይጠቀሙበታል።
- አካቶ
ምንም እንኳን ከምርታቸው ወይም አገልግሎታቸው ጋር ምንም ሕብረት ባይኖረንም አስተዋዋቂዎቹ ‘እኛ’ ወይም ‘የእኛ’ እያሉ ሁሉንም በገዛ ፈቃዳቸው አባላቸው ያደርጋሉ።
- እርጒዝ ቃላት
አደገኛ፣ ከባድ፣ የመጨረሻ፣ ታላቅ፣ ወሳኝ፣ የሞት ሽረት፣ የከፋ፣ ልዩ ወዘተ. . .
- ድግግሞሽ
ቋቅ እስክል ድረስ መደጋገም
- ምስክርነት
መንግሥት ባመቻቸልን ምቹ አጋጣሚ በሳምንት ሦስቴ መብላት ችለናል።
- ትልቅ ውሸት
ካልዋሸህ አይቀር ድብን አድርገህ ዋሽ፣ ከዚያን ሰዎች ያምኑሃል። የሰዎች ሥነ-ልቦና ከትናንሽ ውሸቶች ይልቅ ትላልቅ ውሸቶችን የማመን ዝንባሌ አላቸው። ውሸቱን ታዲያ በሙሉ እርግጠኝነት መናገር፣ ከተቻለ መማል።
2. አትነሣም ወይ
ሀገራችን እስከ መቼ በነዚህ ሰዎች እጅ ትሰቃያለች? ተደፍረና፣ ተንቀናል፣ ብታምኑም ባታምኑም በቊም ሞተናል።
3. የባሰ አታምጣ
ይህንን ድርጅት ቶሎ ካላስወገድን አገሪቱ መቀመቅ ትወርዳለች።
መገምገም (Evaluation)፦ ከመመርመ ቀጥሎ ያለው ሂደት የተገኘውን መረጃ መገምገም ነው። አብዛኛውን ጊዜ የሐሰት መረጃዎች እንኳን እውነት የሚመስሉበት ጊዜ አለ። ወይም የልብ ትርታችንን የሞኰረኲርና ስሜታችንን የሚገዛ ሆኖ ስለሚቀርብ መረጃውን ከመገምገም ይልቅ እንደወረደ ለመዋጥ የምንፈተንበት ጊዜ ይኖራል። ይኸ ማለት ጣፋጭ ውሸትን እንደመጋት ማለት ነው። ለምሳሌ የምንጠላው ወይም የምንቃወመው ሰው ላይ የሚቀርቡ የፈጠራ ክሶች በሚሰራጩበት ጊዜ መረጃው ትክክል ይሁንን ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ ጠላቴ ነው ያለነውን ሰው ወይም ቡድን እንዲያሳጣልን ብቻ ለመቀበል እንገደዳለን። ይህ በሙያዊ ቋንቋ potruth ይባላል። ቃሉ በ2016 ዓ.ም የተፈጠረ ሲሆን ከነባራዊ እውነታ ይልቅ ከታዳሚ ስሜት፣ እምነት ወይም ፍላጐት ጋር የተቆራኙ መረጃዎችን ማቅረብ የሚያመለክት ነው።
ነገር ግን ጠናማ መረጃ አጣርቶ መጠቀም የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ስለ መረጃው ተአማንነት አጥብቆ መጠየቅ ይኖርበታል። የመልእክት አምራቹ ማንነት፣ የመልእክት አምራቹ ከሐሳቡ ጋር ያለው የዕውቀት ደረጃ፣ የወከለው ድርጅት፣ ከዚህ በፊት በዚህ ሰው የተላለፉ እውነተኛ መልእክቶች መኖራቸው፣ ከመልእክቱ ጋር የተያያዙ ምስሎች ወዘት. . . ጒዳዮችን ማረጋገጥ የሚዲያ ግንዛቤ ውስጥ የግምገማ ሂደት ነው። በዚህ ጊዜ ጥልቅ አሳቢ (critical thinker) መሆን ይጠይቃል።
ግምገማ በምናካሄድበት ጊዜ ቀጥሎ ያሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ ያስፈልጋል።
- መልእክቱን የፈጠረው ማን ነው?
- ትኲረትን ለመሳብ የተጠቀሙት ዘዴ ምንድን ነው?
- ሌሎች ሰዎች ከኔ በተለየ መልኲ መልእክቱን እንዴት ሊያዩት ይችላሉ?
- ምን ዐይነት እሴቶች፣ የሕይወት ዘይቤዎች ወይም አመለካከቶች በመልእክቱ ውስጥ ተካትተዋል፣ ወይም ተገድፈዋል?
- መልእክቱ የተላከው ለምንድን ነው?
መፍጠር (Creation)፡– የሚዲያ ግንዛቤ ያለው ሰው ሁሌ የመረጃ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን አምራችም ጭምር ነው። መርጦ መቀበል መቻል አንዱ ክህሎት ሲሆን በተራው ማቀበል መቻል ሌላኛው አስፈላጊ ሂደት ነው። ይህ ደረጃ መረጃ ወይም መልእክት መፍጠር፣ ለመልእክቱ የሚስማማ የሚዲያ ዓይነት ማወቅ፣ ከነዚህ ሚዲያዎች ጀርባ ያለው መሠረታዊ የኮምፕዩተር ቴክኖሎጂ (Algorithms) መረዳትን ይጠይቃል። የተለያዩ መልእክቶች የተለያዩ ዓይነት ሚዲያዎችን ይፈልጋሉ።
መልእክት ለመፍጠር የሚያስፈልጒ ሶፍትዌሮች
- የጽሑፍ ሶፍትዌር፣ ለምሳሌ ማክሮሶፍት ዎርድ
- የድምጽ መቅረጫና ማስተካከያ ሶፍትዌር
- የቪዲዮ መቅረጫ ካሜራ
- የቪዲዮ ማስተካከያ ሶፍትዌር
- የምስል ማቀነባበሪያ ሶፍትዌር
- የስክሪን መቅረጫ ሶፍትዌር
- ኦንላይን መግቢያ ሶፍትዌር
የተስተካከልው የመጨረሻ መልእክት ባሉ የሚዲያ አማራጮች ላይ ማሰራጨት።